Five questions with Johnny Interview About Upcoming movie in Toronto -“Feleg”

ኣምስት ጥያቄ ጆኒ ጋር ( Five questions with Johnny)

This is my interview with An Ethiopian film maker based in Toronto Petros Dejene about his new upcoming movie “Feleg

“ነዋሪነቱ ቶሮንቶ ካናዳ ነው ጴጥሮስ ደጀኔ ይባላል ፥፥ የ ቶሮንቶው ሐዲስ ንጋት የኪነ ጥበብ መድረክ ካፈራቸው መካከል ኣንዱ ነው ጴጥሮስ በኣስደማሚ ኣጫጭር ጽሁፎች እና ግጥሞች እንዲሁም በሚሰጣቸው ሚዛናዊ ሂሶች ይታወቃል ፤፤ ጴጥሮስ ኣሁን ኣዲስ ፊልም ሰርቶ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፥፥

ፈለግ የተሰኘው ፊልም ከኣገሩ ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ተወስዶ በኋላ ማንነቱን ማፈላልግ ስለጀመረ ወጣት ይተርካል ፤፤ ኣምስት ጥያቄ ከ ጆኒ ጋር  በሚለው የ ኢትዮ ፊደል ኣምዴ ጴጥሮስን  ስለ ፊልሙ ኣናግሬዋለሁ እባካችሁኣንብቡት

Please read the interview below . 

ጆኒ :  ኣመሰግናለሁ ጴጥሮስ ስለ ፈለግ ፊልም ንገረን

ጴጥሮስ : ይሄ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የሚሰራ  ‘ፈለግ’ የተሰኘ ፊልም የሚተርከው በሕጻንነቱ በጉዲፈቻ ወደ ካናዳ መጥቶ ወጣት ከሆነ በሁዋላ የስጋ ወላጆቹ በሕይወት እንዳሉ ስላወቀ አንድ ወጣት ነው። ወጣቱ ይሄ አስደንጋጭ ግኝት የፈጠረበትን የማንነት ቀውስ ለመመለስ ወላጆቹን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄድ በሕገወጥ መንገድ ሕጻናትን እየነገዱ ገንዘብ የሚሰበስቡ ሃይሎች በከፍተኛ መልኩ ይታገሉታል። በዚህ ልብ አንጠልጣይ ሂደት የማንነት ኩራት እና ቀውስ፣ የትውልድ ክፍተት፣ የገንዘብን ታላቅ አሙዋሳኝ ሃይል፣ በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ የሚፈጠር የፍቅርን ሁሉን አሳሪነት ከኢትዮጵያ ካናዳ በሚመላለሱ ትእይንቶች ያንጸባርቃል። ይሄ ፊልም በግንቦት  ለሕዝብ የሚቀርብ ሲሆን የካሜራ፣ የመብራት፣ የድምጽ እና የእርማት ስራውን (አጠቃላይ ቀረጻ) አልዩ ፊልም ፕሮዳክሽን የሚሰራው ይሆናል።  አልዩ ፕሮዳክሽን በፊልም ዝግጅት ሰፊ ልምድ ያለው ሲሆን ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ ከ10 በላይ ፊልሞችን አዘጋጅቷል ። በአሁኑ ወቀት የወላፈን ተከታታይ ድራማ አዘጋጅና አቅራቢ ድርጅት ነው። በዘመናዊ መሰራያና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ቀረጻ ለማድረግ ብቁ ድርጅት ነው።

ጆኒ  በ ጉዲፈቻ ዙሪያ ፊልም ለመስራት ያነሳሳህ ምንድነው? 

ጴጥሮስ በዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ ዙሪያ ፊልም ለመስራት ያነሳሳኝ ከግል ልምድ በመነሳት ነው። የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ እህቴ ለሆላንድ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ የማጣራት ጥናት አካሂዳ ነበር። በወቅቱ ከእሷ ያገኘሗቸው መረጃዎች እግጅ አስደንጋጮች ነበሩ። ማለትም እራሱን በጨዋነት የሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ሕጻናትን እንደ ሸቀጥ ለጥቅም ብቻ አስልቶ መነገድ ደረጃ የሚደረስ ዝቅጠት ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። የዚህ ሂደት ተጠቃሚዎች ምስኪን ወላጆችን በማታላል ከፍ ሲልም ደግሞ በማስፈራራትና በጉልበት ልጆቻቸውን በመንጠቅ ለውጪ አቅርቦት ይሚሸጡበት ክስተትን ማየት ልብን የሚሰብር ነበር። እንደ ጸሐፊ ደግሞ እንደዚህ ልብውስጥ የሚዘልቁ ጉዳዮች ሲመጡ ብዕር ማንሳት አይቀሬ ነውና የመጀመሪያ ፍላጎቴ በሰማሁዋቸው ታሪኮች ላይ ተመስርቼ ልብ ወለድ ለመጻፍ ነበር። ሆኖም ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሳልተገብረው ቆይቼ ከዓመት ከስድስት ወር በፊት ለመጻፍ ስነሳሳ ከልብወለድ መጽሐፍ ይልቅ ፊልም ቢሆን ተሰሚነቱ በሃገርም በውጪም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል ብዬ ስላሰብኩ የፊልም ስክሪፒት መጻፍ ጀመርኩ።

 ጆኒ በ ጉዲፈቻ ዙሪያ ያሉ ኣሳዛኝ ክስተቶችን ፊልሙ ይዳስሳል በ መልካም ሁኔታ ህጻናትን በ ጉዲፈቻ የሚያሳድጉ እንዳሉ ሳንዘነጋ ይህ ፊልም ምን ያህል በ ባለሙያ ተተችቷል?

ጴጥሮስ የዚህ ፊልም ጽሑፍ በበርካታ ባለሙያዎች ተኸይሷል። እንደውም የእነዚህ ባለሙያዎች ከጠበኩት በላይ የሆነ አበረታች ግምገማ ነው ስራውን ለመቀጠል ከፍተኛ ስንቅ የሆነኝ። በፊልምም ሆነ በአጠቃላይ የትወናው አለም ውስጥ ፋና ወጊና ፈር ቀዳጅ ከሆነው ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው ከአርቲስት ደበበ እሸቱ  እግጅ አበረታች ግምገማና ሂስ ማግኘት ማለት ለእኔ በጣም ትልቅ ስጦታ ነበር። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና የፊልም ዝግጅት ባለሙያ (ማስተርስ) ዳዊት ላቀው፣ በ’ፈርፎርሚንግ እና ቪዙዋል አርትስ’ ባለሙያ (ቢ ኤ) እና መምህር ምንያህል ተሾመ፣ በቴያትሪካል አርትስ ባለሙያ (ቢ ኤ) እና የአለም ሲኒማ ማኔጀር መስፍን ከበደ፣ ከ10 በላይ ፊልሞች ዳይሬክተርና የሲኒማቶግራፊ ባለሙያ ገብረሕይወት ግብረጨርቆስ፣ በመሪ ተዋናይ ቴዲ (እንግዳሰው ሃብቴ) እና ዳዊት አባተ ወዘተ ተገምግሟል። እዚህ ቶሮንቶ ደግሞ ከሃዲስ ንጋት የኪነጥበብ መድረክ አባላት በባዩ ኪዳኔ እና በኢዮብ ከበደ እንዲሁ አበረታችና ጠቃሚ ሂሶችን አግኝቻለሁ። እነዚህና ሌሎችም ስማቸውን ያልጠቀስኩት ባለሙያዎች ገንቢ ሂስ ለስራው ወሳኝ ስለነበረ ከልብ ላምሰግናቸው ወዳለሁ።

ጆኒ የ ካናዳ ፊልም ተመልካቾች በተለይ ከዚ ፊልም ምን እንጠብቅ?

 ጴጥሮስ የካንዳ ተመልካች በዚህ ፊልም መሳጭና ስሜትን የሚነካ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ታሪክ ያገኛል ብዬ አምናለሁ። ለታሪኩ ዳራ ለመስጠት ያህል ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ብቻ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕጻናት ወደ አሜሪካ በጉዲፈቻ ሄደዋል። ወደ ካናዳ የመጡ ሕጻናት ቁጥር በትክክል ባይታወቅም በርካታ ሺህዎች እንደሚሆኑ መገመት አይከብድም። ብዙ ቅን ካንዳዊያን ለልጅ ካላቸው ፍላጎት በመነሳትና በአጋጣሚውም ወላጅ አልባ የሆኑ እና በችግር የሚማቅቁ ሕጻናትን ለመርዳት እንደኢትዮጵያ ካሉ ድሃ ሃገራት ለማሳደግ ያስመጣሉ። ችግሩ የሚጀምረው ይሄንን ሂደት የሚያስፈጽሙት የምዕራቡ ዓለም ኤጀንሲዎችና ድሃ ሃገሮች ያሉ ወኪሎቻቸው አትራፊ የሆኑ  በዚህ ሂደት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈሰው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላርን እንደትርፍ የሚጋሩ የግል ድርጅቶችና ደላሎች በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም እነዚህ ድርጅቶችን የሚቆጣጠር በቂ ሕግና መመሪያ አለመኖሩ፣ ታዳጊ ሃገር ካሉ ወላጆች ድህነትና መረጃ አለመኖር ጋር ተዳምሮ ሕጻናትን ለአስከፊ ወንጀሎች ያጋልጣቸዋል። ስለዚህ ከካናዳ አኳያ ሲታይ በጉዲፈቻ ልጅ ለማስመጣት የሚወስኑ ወላጆች ምን ያህል በዚህ ሂደት ስላሉ አሰቃቂ ወንጀሎች ያውቃሉ? የካናድ ፖሊሲ አርቃቂዎችስ ምን ያህል ሕግጋትን በማውጣትና በማስፈጸም ድርሻቸውን ተወጥተዋል? ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሕጻናት፣ ወላጆቻቸውና አሳዳጊዎች ላይ ይሄ ሂደት ምን ሊያስከትል ይችላል? የሚለውና የመሳሰሉት በጠቅላላ በካናዳውያን ሊታዩና ሊታሰብባቸው የሚገባ ጉዳዮች ናቸው። ይሄ ፊልም ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እነዚህን ጉዳዮች ይዳስሳል።

ጆኒ ኣሁን በ ከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከተ እና እየተስፋፋ በሚገኘው የ ኣገራችን የፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ያንተ ፊልም የሚያሳየን ኣዲስ ነገር ምን ይሆን?

 ጴጥሮስ ይሄ ፊልም የሚያነሳው አበትይ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በሃገራችን ፊልም ኢንዱስትሪ ያልተዳሰሰና በዓለም አቀፉም ፊልም ብዙ ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ ነው። በፊልሙ ላይ ጉልህ ድርሻ የሚኖራቸው የተወሰኑ ካናዳውያን ተዋናዮች ይኖሩበታል። ከጃንራ አንጻር ስናየው ደግሞ የሀገራችን ፊልሞች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ወይ ኮሞዲ አለበለዚያም ሮማንቲክ ድራማዎች ናቸው። ይሄ ፊልም ግን ድራማ ትሪለር መሆኑም ለየት ያደርገዋል። ትዕይንቱም በትይዩ ከኢትዮጵያ ካናዳ እየተመላለሰ የሚሄድ ሲሆን ከታሪኩ ድንበር ዘለልነት አንጻር ፍላጎቴ እና አላማዬ በዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲታይ ለማድረግ ነው።

በመጨረሻም ይሄንን ፊልም ፋይናንስ የማደርገው በግሌ እንደመሆኑ መጠን ስፖንሰሮች ለማግኘት በመንቀሳቀስ ላይ እገኛለሁ። በተጨማሪም የፊልሙ ጭብጥ ሁላችንንም የሚመለከትና ለሕዝብ እይታ መድረስ ያለበት ቁምነገር ስለሆነ በፌብሩዋሪ 11, 2018  በማዘጋጀው የፈንድ ሬዚንግ አዝናኝ ዝግጅት ላይ ሁሉም ወገን ተገኝቶ አጫጭር ድራማዎችን፣ ልብወለዶችን፣ ግጥሞችን እና ሞኖሎጎችን የቪዲዮ ፕሬዘንቴሽኖችን እየኮመኮመ በመዝናናት እንዲተባበር በትህትና እጋብዛለሁ።

ለተሰጠኝ እድልና ትብብር አመሰግናለሁ!

እኛም በ ኢትዮ ፊደል ስም እናመሰግናለን

Yohannes Ayalew

Related Posts

Leave a Reply

Read also x