Bahir Dar University Awarded Film Makers

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2007 ዓ.ም በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ የተሰሩና በወጥ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀማቸውና ኢትዮጵያዊ የሆነውን ባሕል በማንፀባረቅ ለአማርኛ ቋንቋ እድገት የበኩላቸውን የተወጡ የፊልም ባለሙያዎችንና የፊልም ሥራዎችን በዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ምሁራንና በታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች አስገምግሞ በአሸናፊነት የተመረጡ ፊልሞችን በመሸለም እውቅና ሰጠ።

ታዋቂው የፊልም ስራና የማስታወቂያ ባለሙያ አርቲስት ተስፋየ ዳኘው ለውድድር ስለቀረቡት 5 ፊልሞች ያላቸውን አጠቃላይ አስተያየት ገልፀዋል።

13237791_1071353752940103_3923204590215346978_n

 

ፊልሞቹ በምስል፣ድምፅ፣ የትረካ ዘዴ፣ መብራት መሰረት ተገምግመው “የብራና መንገድ” የተሰኘው የደምስ አያሌው ፊልም 1ኛ በመሆን አሸንፏል።የፊልሙ አዘጋጅም የተዘጋጀለትን ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ እጅ ተቀብሏል።

ዩኒቨርሲቲው ከ1ኛ-5ኛ ለወጡ ፊልሞች የ30ሺህ፣ 20ሺህ፣10ሺህ እና 5ሺህ ብር ሽልማት እንደ ቅደምተከተላቸው አበርክቷል።

በተጨማሪም በስነስርዓቱ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተፃፉ መጽሀፍትን መርጦ ፀሀፊ ደራሲያንን ሸልሟል።

ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪም የአማርኛ ቋንቋን በማስተማር በተማሪዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ከቻሉ የአማርኛ መምህራንንም በማወዳደር እንዲሁ እውቅና መስጠትና የመሸለም ስራ ተሰርቷል።

ዶ/ር ባይሌ ሽልማት በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ቋንቋ የሚያድገው ተጠቃሚዎች ከሚያደርጉት ተግባቦት በተጨማሪ በትምህርት፣በመጽሀፍት ሲፃፍ፣ በፊልም ሲሰራ እና በመሳሰሉት ክንውኖች በመሆኑ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ባለሙያዎችን ከማገዝ አኳያ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን በማመቻቸት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ዶ/ር ባይሌ አክለውም የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ መርሀግብሩ ዩኒቨርሲቲው የአማርኛ ቋንቋ እንዲበለጽግ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልፀው ለወደፊት ሰፋ ባለ ዝግጅት የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለወደፊት በአማርኛ ቋንቋ የሚጽፉ ሰዎችን በህትመት እንደሚያግዝ ዶ/ር ባይሌ ቃል ገብተዋል።

የሽልማትና አውቅና መርሀግብሩን የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም አዘጋጅቶታል።

ምንጭ፡- ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ

Yohannes Ayalew

Related Posts

Leave a Reply

Read also x